
በግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የተግባር ተኮር ስርዓተ ትምህርትን ለማስጀመር ውይይት ተካሄደ።
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ስራ አስፈፃሚዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ ኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች በተገኙበት በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ተግባር ተኮር ስርዓተ ትምህርት (Practice-based curriculum) ማስጀመር ላይ ያተኮረ ወርክሾፕ ህዳር 9/2019 ዓ.ም አካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አንተነህ አገዘው፤ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመተርጎም የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ለማስቻል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ብቻ ሳይወሰኑ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀራረብ ተጨባጭ ችግሮችን እንዲለዩና መፍትሄ እንዲያመነጩ ማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑንም ጠቁመዋል። ተግባር ተኮር አካሄድን መከተል ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ስራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪና ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያስችልም በመግለጽ፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና አመራር ለስርዓተ ትምህርቱ ተግባራዊነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ቁልፍ ንግግር (Keynote Speech) ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አለማየሁ ቢሻው፣ ቦርዱ የተግባር ተኮር ትምህርት በአፋጣኝ እንዲተገበር አቅጣጫ መስጠቱን አውስተው፣ የሚሰጠው የትምህርት ይዘት ከየት እንደመጣና ወደ ተግባር እንዴት እንደሚተረጎም በጥልቀት ሊፈተሽ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። ወደ ተግባር የማይተረጎም የትምህርት ይዘት የሚፈለገውን ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ ትምህርት የተማሪዎችን የማመዛዘን አቅም የሚያዳብርና ተግባራዊ ብቃትን የሚያላብስ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ፕሮፌሰሩ በትምህርት ሂደት ውስጥ የሚፈጠር የአስተሳሰብና የነርቭ ትስስር (Neural connection) ተማሪዎች እውቀትን ከተጨባጭ ህይወት ጋር እንዲያዋህዱ ወሳኝ ሚና እንዳለው አብራርተዋል። በተግባር ተኮር ትምህርት ላይ የሚስተዋለውን የመምህራን እጥረት ለመቅረፍ በአካባቢው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችን መጠቀም እንደሚገባና ቀጣይነት ያለው የማህበረሰብ ተሳትፎ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ለዚህም ስትራቴጂ ተቀርጾ በዩኒቨርሲቲው ሴኔት እንዲጸድቅና በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባ አሳስበዋል።
በወርክሾፑ ላይ የዩኒቨርሲቲው የእፅዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር አራጋው ገ/ማርያም በግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ስር ባሉ ትምህርት ክፍሎች ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተግባር ተኮር ትምህርትን በማካተት ዙሪያ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል። መ/ር አራጋው እንደገለጹት፣ ተግባር ተኮር አሰራር የተቋሙንና የማህበረሰቡን ሁለገብ ትስስር ለመፍጠርና ለማጠናከር፣ እንዲሁም በተግባር የተፈተኑ ብቁ ምሩቃንን ለማፍራት ወሳኝ ሚና አለው። የመነሻ ጽሑፉ ያሉትን ጸጋዎችና መልካም አጋጣሚዎች፣ እንዲሁም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያካተተ ሲሆን፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥብቅ ትስስር መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል።
በቀረበው ሐሳብ ላይ የተወያዩት ተመራማሪዎችና መምህራን፣ ተማሪዎች ከግቢ ውስጥ ስልጠና ባለፈ ወደ ማህበረሰቡ ወርደው ተጨባጭ ችግር ፈች ስራዎችን እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል። ለዚህም ተቋሙ አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላትና እንደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና መሰል ተቋማት መልካም ልምዶችን በመውሰድ የተማሪዎችን ውጤት ለአገር ውስጥና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ማስተዋወቅ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በማጠቃለያ ንግግራቸው ዶ/ር አንተነህ አገዘው፣ ተግባር ተኮር ትምህርትን በተሳካ ሁኔታ ለመጀመር ያሉትንና የጎደሉትን ግብዓቶች በሚገባ መለየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ለዚህም በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት በኩል ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ያሉ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ፣ የአፈር ምርመራ ላቦራቶሪ፣ ወተት ልማት እና የ”ባዮፊውል” ማመንጫ ግንባታዎች፣ እንዲሁም የመስኖ፣ የንብ ርባታ ማስፋፊያና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎችን አብራርተዋል። በተጨማሪም በመማር ማስተማር ሂደቱ የንድፈ ሀሳብ ትንተናን ከመጠቀም ባለፈ፣ ተግባር ተኮር የምዘና ዘዴዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ህዳር 10/2019 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
For the latest updates:
🌐 Website: http://www.dku.edu.et
📘 Facebook: https://www.facebook.com/Debarkuniversityandcollegeofficial
🐦 Twitter: https://twitter.com/DebarkUniETH
📲 Telegram: https://t.me/+Ed4_Lp3bywo4MzI0
📹 YouTube: https://www.youtube.com



