
በግብርና ዘርፍ እየተሰሩ የሚገኙ የጥናት ምርምር፣ ቴክኖሎጅ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ጉብኝት ተካሔደ፡፡
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ካውንሰል አባላት በ2018 ዓ.ም ተጀምረው ወደ 2019 በጀት ዓመት የተሻገሩ የማህበረሰቡን አኗኗርና ህይወት ለመቀየር የሚያግዙ የግብርና የምርምር፣ ቴክኖሎጅ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ጥቅምት 06/2019 ዓ.ም በመስክ ተመልክተዋል፡፡
በአካዳሚክ፣ምርምር፣ቴክኖሎጅ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ል ፕሬዚዳንት ልዩ ረዳት በዶ/ር መዝገበ ማንመክቶ መሪነት የተካሄደው፤ይህ የተለያዩ የግብርና ምርምር ፕሮጀክቶች ቀጥተኛ ጉብኝት ፕሮጀክቶቹ ከተቀመጡላቸው ግቦች አንፃር የደረሱበትን ደረጃ በመገምገም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያግዙ እርምጃዎችን ለመውሰድ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡
በመስክ ምልከታ መርሃ-ግብሩ ከዳባት ወረዳ ወቅን ቀበሌ ፍኖተሰላም የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከል በ1.75 ሄክታር ማሳ በሶስት የስንዴ ዘር ብዜት የምርምር ስራዎች እና ጉደኔ በተባለ የድንች ዘር ማስፋት የተቀረፀ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት ተጎብኝተዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በቅርቡ የደባርቅ ከተማ አስተዳደር አካል በሆነው ምቃራ ቀበሌ በገበሬዎች ማሳ ላይ በተለያዩ የምርምር ሀሳቦች በቢራ ገብስ፣ በተለየያዩ አዳዲስ የስንዴ እና የአብሽ ሰብሎች እንዲሁም በካሮት እና ቀይ ሽንኩርት ዘር ብዜት እየተሰሩ ያሉ የተግባራዊ ምርምር ፕሮጀክቶች ተጓብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ በተመረጡ ገበሬዎች እየተዘጋጁ ያሉ የቨርሚ ኮምፖስት ስራዎችም በምርምር ካውንስል ሉካን ቡድን አባላቱ ምልከታ ተደርጎባዋል፡፡ በጉብኝቱ መጨረሻ በተደረገ ግምገማዊ ውይይት ፕሮጀክቶቹን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፤በርካታ የግልፀኝነት ጥያቄዎችም ተነስተው በተመራማሪ መምህራን በኩል ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በወይይቱ ሂደቱ ዶ/ር መዝገበ ማንመክቶ የማጠቃለያ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ዶ/ር መዘገቡ በሰጡት አስተያየት ተመራማሪ መምህራን በወቅታዊ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ የተለያዩ የሰብል በሽታዎችን ሊቋቋሙ የሚችሉ እና በተሻለ ሁኔታ ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን በማቅረብ የገበሬውን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር እያደረጉት ላለው ጥረት የምስጋና እውቅና ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም በተበታተነ መልኩ እየተሰሩ ያሉ የምርምር ሀሳቦችን ወደ አንድ ፓኬጅ በማምጣት፤ያላስፈላጊ ድካምን እና ወጭን ለመቀነስ መሰራት እንዳለበት በመጠቆም የተቋሙ ማኔጅመንት አባላት ሂደቱን ለማሳለጥ ተገቢውን እገዛ እንደሚያደረጉ አረጋግጠዋል፡፡
ጥቅምት 07/2019 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
For the latest updates:
🌐 Website: http://www.dku.edu.et
📘 Facebook: https://www.facebook.com/Debarkuniversityandcollegeofficial
🐦 Twitter: https://twitter.com/DebarkUniETH
📲 Telegram: https://t.me/+Ed4_Lp3bywo4MzI0
📹 YouTube: https://www.youtube.com



