
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ እያቋቋመ በሚገኘው የአትሌቲክስ ምርምርና ስልጠና ማዕከል ዙሪያ ሀገራዊ የምክክር ወርክሾፕ አካሄደ
ሰሜን ጎንደርና አካባቢው ከባህር ወለል በላይ የሚገኝበት ከፍታ እና ተስማሚ የአየር ንብረትን መሠረት በማድረግ ዩኒቨርስቲያችን እያቋቋመ በሚገኘው አዲስ የአትሌቲክስ ምርምርና ስልጠና ማዕከል ዙሪያ ያዘጋጀው ሀገራዊ የምክክር ወርክሾፕ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።
በዚሁ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፣ በፌደሬሽኑ የስልጠናና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አሰፋ በቀለ፣ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ም/ል ኃላፊ አቶ አዱኛ ይግዛው፣ የአማራ ክልል አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘላለም መልካሙ እና የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሃኔ ጌትነት፣ ታዋቂ አትሌቶችና የአቻ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማማው ዘገዬ፤ ዩኒቨርሲቲውና አካባቢው የሚገኝበት መልካምድራዊ አቀማመጥ ለአትሌቲክስ ስፖርት ስልጠና እጅግ ተስማሚና ተፈጥሯዊ ጸጋ የተላበሰ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም ከትምህርት ሚኒስቴር አገራዊ አቅጣጫ አንጻር አትሌቲክስን የተቋሙ የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) ለማድረግ የታለመ ሲሆን፣ ማዕከሉን ከስፖርት ቱሪዝም ጋር በማያያዝ የሰሜኑን አካባቢ ተፈጥሯዊ ጸጋ የማልማትና የማስተዋወቅ ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመዋል። በመሆኑም በረጅም ጊዜ ዕቅድ አካባቢውን የአትሌቲክስ ስፖርት ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራና በቅርቡ ወጣት አትሌቶችን በመቀበል ሥራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
በወርክሾፑ ላይ የማዕከሉን አጠቃላይ የዕቅድ ሰነድ ያቀረቡት የማዕከሉ አስተባባሪ መ/ር አዱኛ ደረሰኝ እና የማዕከሉ የስልጠና ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ሲሳይ ፈንታ፤ ማዕከሉ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን፣ የምርምር ሥራዎችን፣ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችንና የአሠራር ማዕቀፎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀረቡት ሰነዶች፣ መተዳደሪያ ደንቦችና ስትራቴጂያዊ እቅዶች ሰፊ ወይይት የተደረገ ሲሆን ከመድረኩ ሰፊ ማጠቃለያና አቅጣጫ ተሰጥቷል። በመድረኩ ላይ ተገኝተው ገንቢ ሙያዊ ምክረ-ሀሳብ ያቀረቡት ዶ/ር ዘላለም ማዕከሉ በይፋ እንዲቋቋም የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ አመራሮች አድንቀዋል። ማዕከሉ በስትራቴጂያዊ መንገድ መዋቀሩ ተቋሙ የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚያስችለውም አመልክተዋል።
ዶ/ር አንተነህ አገዘው በበኩላቸው ለመድረኩ ተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበው፤ የተቋሙ ማኔጅመንት ማዕከሉን ውጤታማ ለማድረግ ያለውን ጽኑ ውሳኔና ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። አያይዘውም አዲሱ ማዕከል ትምህርት ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ የጀመረውን ሁለንተናዊ የትምህርት ሥርዓት ሪፎርም መሬት ለማውረድና ዩኒቨርሲቲው በተቋማት መለየት የተሰጠውን ተልዕኮ በውጤታማነት ለመወጣት እንደ ዋና ማስፈጸሚያ መሣሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል። በተለይም ማዕከሉ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ፣ ሥርዓተ-ትምህርትን ከገበያ እና ከሀገር ፍላጎት ጋር በማቀናጀት ተቋሙ በተሰማራበት የልዩነት መስክ (Differentiation Track) ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት በሚያደርገው ጉዞ ላይ ቁልፍ የአቅም ግንባታ ሚና እንደሚጫወት ዶ/ር አንተነህ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጋሻው ግስሙ፤ ተቋሙ የአትሌቲክስ ምርምርና ስልጠና ማዕከል መቋቋም የአካባቢውን ከፍተኛ ቦታ መገኘት መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በውይይቱ ከተሳታፊዎች የተገኙ ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ግብዓቶችንና ምክረ-ሀሳቦችን በመጠቀም ማዕከሉን በስኬት ለማንቀሳቀስ እንደሚሰራ በመግለጽ ወርክሾፑ መጠናቀቁን አብስረዋል።
ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
For the latest updates:
🌐 Website: http://www.dku.edu.et
📘 Facebook: https://www.facebook.com/Debarkuniversityandcollegeofficial
🐦 Twitter: https://twitter.com/DebarkUniETH
📲 Telegram: https://t.me/+Ed4_Lp3bywo4MzI0
📹 YouTube: https://www.youtube.com



