
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ የ2019 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ገመገመ
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ የ2019 ዓ.ም የመጀመርያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ትላንት ጥቅምት 22/2019 ዓ/ም በዝርዝር ገምግሟል። ቦርዱ በሩብ ዓመቱ በመማር ማስተማር ሒደት እና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተሰሩ ሥራዎችን እንዲሁም የተማሪዎችንና መምህራንን የምርምር ሥራዎች ጅማሮዎች በበጎ ጎኑ አድንቋል።
የቦርድ ሰብሳቢው ክቡር ዶ/ር አክሊሉ ታደሰ እንደገለጹት፤ በትምህርት ጥራት ዙሪያ የተሰሩ አበረታች ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸው፣ የመማሪያ ክፍሎችንና የቤተ-ሙከራዎችን (Labs) አቅም በማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋፋት እንዲሁም የመምህራንን የክህሎት ማሻሻያ ስልጠናዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የትምህርት ጥራትን ይበልጥ ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሥርዓተ-ትምህርት ክለሳ በማድረግ፣ የተማሪዎችን የተግባር ትምህርት የሚደግፉ ሥርዓተ-ትምህርቶችን መቅረጽና መተግበር ላይ በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በምርምር ዘርፍም የተጀመሩ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችና የፈጠራ ግኝቶች ተደራሽነታቸው እንዲሰፋና በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ሊያገኙ በሚችሉ ሳይንሳዊ ጆርናሎች ላይ እንዲታተሙ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በተጨማሪም የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች በትክክል የማህበረሰቡን ተጨባጭ ችግር የሚፈቱና ከተገልጋዩ ማህበረሰብ ጋር በቀጥታ ሊያገናኙ በሚችሉ ስልቶች ተቀርፀው መመራት እንዳለባቸው ቦርዱ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን መነሻ በማድረግ በዩኒቨርሲቲው ሥር የተቋቋመው የሰሜን ተራሮች ምርምር ኢንስቲትዩት (SMRI) ላይ እየተሰሩ ያሉና ለመስራት የታቀዱ ሐሳቦች ስትራቴጂካዊና አግባብነት ያላቸው በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ቦርዱ አጽንኦት ሰጥቷል።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ-ገዝነት (Autonomy) ለሚያደርገው ጉዞ አጋዥ ስለሆነው የራስ ደጀን የንግድ እና ማማከር ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ የተሰሩት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን የገለጹት ክቡር ዶ/ር አክሊሉ፤ ኢንተርፕራይዙ ለቀጣይ ወደ ግዙፍ አገራዊና ክልላዊ ፕሮጀክቶች መግባት እንዳለበትና እውነተኛ የተማሪዎች የተግባር ትምህርት መለማመጃ እንዲሆን በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በቦርዱ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር አስማማው ዘገየ ዝርዝር መልስና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥ ከተሰጡት አቅጣጫዎችና ግብዓቶች መነሻነት በቀጣይ ሩብ ዓመታት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ተቋሙ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ጥቅምት 23/2019 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
For the latest updates:
🌐 Website: http://www.dku.edu.et
📘 Facebook: https://www.facebook.com/Debarkuniversityandcollegeofficial
🐦 Twitter: https://twitter.com/DebarkUniETH
📲 Telegram: https://t.me/+Ed4_Lp3bywo4MzI0
📹 YouTube: https://www.youtube.com



