
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የተማሪዎችን ቅበላ፣ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎችን ቁመና ገመገመ።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ የካውንስል አባላትና ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት፣ አዲሱን የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች የመጨረሻ ደረጃ ግምገማ ስብሰባውን ዛሬ መስከረም 22/2019 ዓ.ም አካሂዷል።
በስብሰባው ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማማው ዘገዬን ጨምሮ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ሥራ አስፈጻሚዎችና የሥራ ሂደት አስተባባሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ ተቋሙ ከመስከረም 25/2019 ዓ.ም ጀምሮ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ያደረጋቸውን አጠቃላይ ዝግጅቶች በዝርዝር ገምግመዋል።
በግምገማውም የመማር-ማስተማር ሂደት ዝግጅትን በተመለከተ የመማሪያ ክፍሎች፣ የቤተ-ሙከራዎችና የቤተ-መጻሕፍት ዝግጅት ያለ ምንም መስተጓጎል ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኙ ተረጋግጧል። እንዲሁም ከተማሪዎች አገልግሎትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች አንጻር የተማሪዎች ምግብ ቤት፣ የመኝታ ክፍሎች፣ የክሊኒክ አገልግሎቶች ዝግጁነት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ታይቷል።
በስተመጨረሻም በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ሰላማዊ፣ ስኬታማና የተቀናጀ የመማር-ማስተማር ሂደት እንዲኖር የጋራ የሥራ መመሪያ የተቀመጠ ሲሆን፤ ሁሉም አመራሮችና የካውንስል አባላት የተጣለባቸውን ተቋማዊ ኃላፊነት በከፍተኛ ትጋት እንዲወጡ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
መስከረም 22/2019 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
For the latest updates:



