
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በድርቅ ለተጎዱ የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች ድጋፍ አደረገ።
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ጎንደር ዞን በጠለምት ወረዳ በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሆን ሁለንተናዊ የአይነት ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉ በዩኒቨርሲቲው የተመረተ የምግብ እህል እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ኢንተርፕራይዝ ማተሚያ ቤት የተዘጋጁ የተማሪ ደብተሮችን ያካተተ ነው።
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር መ/ር ጌታቸው ውለታው የተመራው ልዑክ ቡድን መስከረም 11/2019 ዓ.ም በወረዳው በአካል በመገኘት ድጋፉን ለማህበረሰቡ አስረክቧል።
ዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ባደረገው በዚህ ድጋፍ በድርቅ ምክንያት ችግር ውስጥ ለወደቁ በወረዳው የመረው ብላ እና መረው ገብርኤል ቀበሌዎች ለሚገኙ 532 የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሆን 80 ኩንታል የምግብ እህል አከፋፍሏል።
በተያያዘም በድርቁ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ልጆች ማለትም በመረው ብላ እና መረው ገብርኤል ቀበሌዎች ለሚገኙ 4 ትምህርት ቤቶች የሚሆን 76 ደርዘን ደብተር ማስረከቡ ተገልጿል።
የወረዳው አመራሮችና የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በዚህ አስቸጋሪ የድርቅ ወቅት ያደረገላቸው ድጋፍ ትልቅ አለኝታነቱን ያሳየበትና ችግራቸውን ያቀለለ በመሆኑ ላደረገው ድጋፍ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
መስከረም 12/2019 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
For the latest updates:



