
በበጀት ዓመቱ የመማር-ማስተማር ሥራ አጀማመር ዙሪያ ከመምህራን ጋር ውይይት ተካሄደ።
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ወር መጨረሻ ተማሪዎችን ለመቀበል ጥሪ ማድረጉን ተከትሎ፣ በበጀት ዓመቱ የመማር-ማስተማር ሥራ አጀማመር ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ውይይት ከመምህራን ጋር ትላንት መስከረም 13/2019 ዓ.ም አካሂዷል።
የተቋሙን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ግልጽ በማድረግ የበጀት ዓመቱን የመማር-ማስተማር፣ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት ለማሳለጥ በተዘጋጀው በዚህ መርሃ-ግብር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ አስተባባሪዎች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና መምህራን ተሳትፈዋል።
በሂደቱም ባለፈው ዓመት ከሶስቱም ዘርፎች የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራትን፣ ያጋጠሙ ችግሮችን እና ከተቋሙ የለውጥ ፍላጎት አንፃር በትምህርት ዘመኑ በትኩረት እንዲከናወኑ የተለዩ ነጥቦችን በወፍ በረር የሚያስቃኝ መነሻ ሪፖርት በአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ልዩ ረዳት በዶ/ር መዝገቡ ማንመክቶ አማካኝነት ቀርቧል።
ታዳሚዎች የቀረበውን መነሻ ሪፖርት እንዲሁም አጠቃላይ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ተቋሙን ተመራጭ ለማድረግ የሚያግዙ ምሁራዊ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን፣ መሰረታዊ ጥያቄዎችንም አንስተዋል። ለተነሱት ጥያቄዎች በሚመለከታቸው የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከፍተኛ አመራሮች ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በተደረገው ውይይት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ለ2019 በጀት ዓመት የሥራ ስኬት የሚረዱ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡ ሲሆን፤ በተለይም የመማር-ማስተማር ሂደቱን ጥራት ማረጋገጥ፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራትን ከተቋሙ የለውጥ ፍላጎት ጋር ማጣጣም፣ የውስጥ አሠራርና አገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍ እንዲሁም ተቋማዊ ገጽታና ተደራሽነትን (Visibility) ለማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በተዋረድ የሚገኘው አመራርና መምህራን የተጣለባቸውን ኃላፊነት በየደረጃው በግንባር ቀደምትነትና በተጠያቂነት ስሜት መወጣት እንደሚገባ የገለፁት አመራሮቹ፤ በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ማነቆዎችንና ጉድለቶችን ሳያዘገዩ ወዲያውኑ በመጠቆም ፈጣን እርማት እንዲደረግላቸው ማድረግ እንደሚገባ አስምረውበታል።
በተያያዘም፣ ወደ አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚደንትነት ለተዛወሩት ለዶ/ር ጋሻው ግስሙ በአካዳሚክ ዘርፉ ላበረከቱት ጉልህ አስተዋፅኦ በዶ/ር አንተነህ አገዘው አማካኝነት የእውቅና ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ዶ/ር ጋሻውም ስለተደረገላቸው እውቅና ምስጋና አቅርበው በአዲሱ ኃላፊነታቸውም የአካዳሚክ ዘርፉን በመደገፍ የተቋሙን ገጽታ ለማሳደግ የድርሻቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
መስከረም 14/2019 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
For the latest updates:



