
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ሞዴል የማህበረሰብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግበት የቆየውን ዘመናዊ የማህበረሰብ የመጀመሪያ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት ዛሬ መስከረም 11/2019 ዓ.ም በይፋ ሥራ አስጀምሯል።
በቦታው ተገኝተው የመማር ማስተማር ሂደቱን እና አጠቃላይ ሁኔታውን የተከታተሉት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ተወካይ ዶ/ር አንተነህ አገዘው፤ የትምህርት ቤቱ ሥራ መጀመር የዩኒቨርሲቲው የረጅም ጊዜ እቅድ ፍሬ ያፈራበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ብቻ ሳይወሰን የመጀመሪያ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት መክፈቱ፣ ትውልድን በእውቀትና በክህሎት ለመቅረጽ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ዶ/ር አንተነህ አያይዘውም፣ ትምህርት ቤቱ የዩኒቨርሲቲው አካል እንደመሆኑ መጠን ከተለመደው አሰራር ወጣ ባለ መልኩ የላቀ የትምህርት ውጤት፣ ከፍተኛ የፈጠራ አቅም እና ክህሎት የሚገነባበት ማዕከል እንዲሆን አሳስበዋል።
ከትምህርት ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ተቋሙ ቅድመ-ዝግጅቱን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ በ11 መምህራን አማካኝነት 56 የ1ኛ ክፍል እና 30 የ2ኛ ክፍል በድምሩ 86 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን ጀምሯል። ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት የቅድመ-አንደኛ ደረጃ (KG) ትምህርት ማስጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮ ወደ 1ኛ ክፍል ከተሸጋገሩት ተማሪዎች በተጨማሪ የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርቱም በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል።
በአሁኑ ወቅት በቅድመ-አንደኛ ደረጃ (KG) ዘርፍ በKG 1 (86)፣ በKG 2 (154) እንዲሁም በKG 3 (49) ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 289 ህፃናት በ16 መምህራን አማካኝነት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
መስከረም 11/2019 ዓ.ም
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
For the latest updates:













