
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የ2018 ዓ.ም የሁለተኛ ዙር ተመራቂ ተማሪዎቹን በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመረቀ።
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት መርሐ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሰኔ 20/2018 ዓ.ም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል። በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ የተመራቂ ወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ በዕለቱ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ 121 ሴት እንዲሁም 181 ወንድ በድምሩ 302 ተማሪዎች ተመርቀዋል።
በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የተከበሩ አቶ ባያብል ሙላቴ ለተመራቂዎች መልካም ምኞታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ተመራቂዎቹ በቀጣይ የሕይወትና የሥራ ምዕራፋቸው ላይ ሊከተሏቸው የሚገቡ እጅግ ጠቃሚ ምክሮችን አበርክተዋል።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገዬ (ዶ/ር) ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ተማሪዎች ለዚህ ስኬት ለመብቃት ያሳለፏቸውን ውጣ ውረዶች አስታውሰዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም “በትምህርት ቆይታችሁ ያጋጠሟችሁን ችግሮች ለመቋቋም ያሳያችሁት ጠንካራ መንፈስና የከፈላችሁት መስዋዕትነት ለቀጣዩ ሕይወታችሁ ትልቅ ስንቅ ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህንኑ ፅናት በመድገም ለሀገርና ለማኅበረሰብ ልማት እንድትተጉ” በማለት አሳስበዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ት ዶ/ር ጋሻው ግስሙ (ተወካይ) የኮሌጆችን፣ የትምህርት ክፍሎችን እንዲሁም በአጠቃላይ የከፍተኛ ውጤት (የሜዳሊያና የዋንጫ) ተሸላሚ ተማሪዎችን ይፋ አድርገዋል።
በዚህም መሠረት፦
ተማሪ ንብረት ሀብታሙ በ3.97 ውጤት በአጠቃላይ የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን፣
ተማሪ ቤተልሔም ካሴ ደግሞ በ3.95 ውጤት የሴቶች ዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች።
እነዚህ ሁለቱም የዋንጫ ተመራቂ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በጤና ሳይንስ ኮልጅ ስር ካስመረቃቸው የነርሲንግ ትምህርት ክፍል የተገኙ መሆናቸው ተገልጿል።
በዋልያ ሙዚቃ ባንድ የታጀበው ይኸው የምረቃ ፕሮግራም፤ በከፍተኛ አመራሮች ንግግር ፣ በዋና ሬጅስትራር ጽሕፈት ቤት ሪፖርትና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች በተበረከተ የሜዳሊያ ሽልማት ደምቆ ውሏል።
ሰኔ 20/2018 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ



