
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ “ራስ ደጀን ንግድና ማማከር ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ” ተስፋ ሰጪ የንግድና የገቢ ማመንጨት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ ታወቀ።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቢ ማስገኛ ኢንተርፕራይዞች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 66 እና በኢንተርፕራይዞች ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 450/2012 መሠረት ያቋቋመው “ራስ ደጀን ንግድና ማማከር ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ” ከምስረታ ጊዜ ጀምሮ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቶ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መግባቱ ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው የውስጥ ገቢ አቅሙን በማሳደግ የመማር–ማስተማርና የምርምር ተልዕኮዎቹን የበለጠ ለማስፈጸም፤ እንዲሁም በሂደት ተቋሙ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያደርገውን ጉዞ ለማፋጠን ኢንተርፕራይዝ ማቋቋሙን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማማው ዘገዬ ገልጸዋል ።በተጨማሪም የኢንተርፕራይዙ መመሰረትና ወደስራ መግባት በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና በአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ዶ/ር አስማማው ጠቁመዋል።
የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አይቶልኝ ሙሌ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት አቅሙን አጠናክሮ በሦስት ዋና ዋና የሥራ ዘርፎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል። በኮንስትራክሽን ዘርፍ በጠቅላላ ሥራ ተቋራጭነት (GC Grade 4) የንግድ ፈቃድ በማውጣትና በኢ-ጂፒ (e-GP) በመመዝገብ ለጨረታዎች ብቁ የሆነ ሲሆን፤ በቅርቡም የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ያወጣውን የአጥር ግንባታ ጨረታ አሸንፎ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቋል። በተጨማሪም በወፍዳር ቀበሌ ድልድይ ፕሮጀክት ተረክቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል። የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማጠናከር ከቡና ባንክ ጋር በተደረገ የብድር ውል ሁለት የ2025 ምርት ዘመናዊ ሲኖትራኮች እና አንድ ሎደር ገዝቶ ወደ ሥራ በማስገባት በኪራይ አገልግሎት አበረታች ገቢ ማስገኘት ችሏል።
አቶ አይቶልኝ አክለው እንደገለጹት፤ ኢንተርፕራይዙ በሌሎች የሥራ ዘርፎችም የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀ ሲሆን፣ በሕትመት ሥራ ዘርፍ ዘመኑ ያፈራቸውን ማሽኖች በመትከልና የሙከራ ሥራዎችን በማጠናቀቅ የማንኛውንም ዓይነት የሕትመት ትዕዛዞች ለመቀበል ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ሆኗል። በተመሳሳይ መልኩ በእንጨትና ብረታብረት ውጤቶች ዘርፍ ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለደንበኞች ማቅረብ ጀምሯል።
በቀጣይም ኢንተርፕራይዙ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት የማማከር ሥራዎችን፣ የሳሙናና ጽዳት ዕቃዎች ማኑፋክቸሪንግን፣ የእንስሳት መኖ ማቀነባበርና ማድለብን፣ የቱሪዝምና የጉዞ ውክልና አገልግሎትን፣ የሞዴል ፋርማሲና መድኃኒት አቅርቦትን፣ የእርሻ መካናይዜሽንን እንዲሁም የመምህራንና ሰራተኞች የካፌና መዝናኛ አገልግሎቶችን ለማስጀመር በትጋት እየሠራ ይገኛል።
መስከረም 5/2019 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
For the latest updates:

















