
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ራስ ደጀን ቃል-ኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክት የትውውቅና ፊርማ ስነ-ስርዓት ተካሄደ
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በወሰደው ተሞክሮ መነሻነት በሰላም ሚኒስትር እና በትምህርት ሚኒስትር በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲተገበር አቅጣጫ መሰጠቱን ተከትሎ፤ “ራስ ደጀን የቃል-ኪዳን ቤተሰብ ትስስር” መፈጠሩን የሚያበስር የመጀመሪያ ዙር የትውውቅና ፊርማ ስነ-ስርዓት ህዳር 28/2018 ዓ.ም አካሂዷል፡፡
በመርኃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የደባርቅ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ጌትነት ፀጋዬ፣ ስራ አስፈፃሚዎችን እና ዳይሬክተሮችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት፣ ከደባርቅ ከተማ ሶስቱም ቀበሌዎች እና ከሁለቱ ቤተ እምነቶች (ከክርስትና እና እስልምና) የተወጣጡ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወላጆች እንዲሁም ተማሪዎች ተገኝተዋል።
በመርሃ-ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት አስማማው ዘገዬ(ዶ/ር) የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው ጥሪውን ተቀብለው ተማሪዎችን በቃል-ኪዳን ልጅነት የመንከባከብ ኃላፊነት ለመውሰድ የተገኙ የደባርቅ ከተማ ማህበረሰብ አባላትን እና የፕሮጀክቱን ተጠቃሚ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ፤ ፕሮጀክቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮን በመቀመር፤ በሰሜን ጎንደርና አካባቢው ማህበረሰብ የእንግዳ ተቀባይነት ባህላዊ እሴት ታግዞ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ሂደትና አተገባበር ከዚህ ደረጃ እንዲደርስ ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የኮሚቴ አባላት ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ዶ/ር አስማማው፤ ሂደቱን በታሰበው ልክ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ ቀጣይነት ያላቸው መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ የውይይት መርሃ-ግብሮችን ለማድረግ ዩኒቨርሲቲያችን በቁርጠኝነት ይሰራልም ብለዋል፡፡
ሥነ-ስርዓቱን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የደባርቅ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ጌትነት ፀጋዬ በበኩላቸው ተማሪዎች ደባርቅ ከተማ እና አካባቢው ያልተበረዘ የእንግዳ አቀባበል ባህል ያላቸው የማህበረሰብ አካላት ባለቤት መሆኑን ተገንዝበው ያለምን መሸማቀቅ ወደ ሁለተኛ ቤተሰባቸው እንደመጡ ተሰምቷቸው ለትምህርታቸው ብቻ ትኩረት እንዲሰጡ በማሳሰብ፤ ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
በጥበብ ቤተሰብ ተማሪዎች ሙዚቃ እየተዋዛ የተካሄደው፤ ይህ የራስ ደጀን ቃል-ኪደን ቤተሰብ ትስስር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር የትውውቅ እና የፊርማ ሥርዓት መርሃ-ግብር ሂደቱን በሚገልፅ ሁኔታ ሪፖርት፣ በተሳታፊዎች አስተያየት እና በቃል-ኪዳን ቃለ መሀላ የታጀበ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡
ህዳር 28/2018 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ



