
የህልውና አደጋ በተደቀነበት በብርቅየው ዋሊያ አይቤክ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ”ዋልያን ከመጥፋት እንታደግ” በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሰሜን ጎንደር ዞን፣ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አጎራባች ወረዳና ቀበሌ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የውይይት መርሃ-ግብሩን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የአካዳሚክ፣ምርምር፣ማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጅ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጋሻው ግስሙ የመድረኩ አላማ ብርቅየው ዋልያን ከተጋረጠበት የመጥፋት አደጋ ለመታደግ


ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ፤ አማራጭ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመለየት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ጋሻው አያይዘው ዋልያ በእኛ ዘመን ቢጠፋ በታሪክ ተወቃሽ እንደምንሆን አስበን በአግባቡ በመጠበቅ ለትውልድ የማሻገር ኃላፊነታችን መወጣት ይገባል ብለዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን አመሰራረት፣በውስጡ የሚገኙ የእንስሳት እና እፅዋት ብዝሃ ህይወት ዓይነቶች እና ለዋልያ የመጥፋት አደጋ መነሻ የሆኑ ችግሮችን የሚያስቃኝ በዩኒቨርሲቲው የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል የተዘጋጀ ፅሁፍ ቀርቧል፡፡
በቀረበው ፅሁፍ እና በአጠቃላይ በዋልያ ላይ እየደረሱ ባሉ የመጥፋት አደጋዎች መነሻነት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱም የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን በተለይ የሀይማኖት አባቶች የዋልያ ግድያን ማውገዝ እንዳለባቸው ተመላክቷል።

ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት በውይይቱ የተነሱ የመፍትሄ ሀሳቦችን በመተግበር የፓርኩን ህልውና በተለይም ብርቅየው ዋልያን ከመጥፋት አደጋ ለመታደግ የበኩላቸውን ለመወጣትና በቅንጅት ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡
ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ