
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የባህል ቀን(Culture Day) አከበሩ
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የባህል ቀንን የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ሰኔ 1/2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።
በዝግጅቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ል ፕሬዚዳንት ዶ/ጋሻው ግስሙ ተማሪዎች የባህል ቀን ማክበራቸው የመጡበትን ባህል የሚያስተዋውቁበት እና የባህል የብዝሃነትን የሚረዱበት እድል የሚፈጥር መሆኑን በመጥቀስ የህይወታቸው አንዱ መልካም አጋጣሚ አድርገው ሊወስዱት እንደሚገባ ተናግረዋል ።
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ የባህል ማዕከል ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን ያከሉት ዶ/ር ጋሻው ፤ ባህልን በማስተዋወቅ በኩል በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

በዕለቱ በዓሉን አስመልክቶ የአንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር ወርቅነህ ሰማቸው ባህልን የተመለከተ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን የባህል ቀኑ የኢትዮጵያን ብዝሃነት በሚያሳዩ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ዘፈን፣ግጥም፣መነባንብ እና በሌሎች ተማሪዎች ባዘጋጇቸው የጥበብ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በተያያዘ በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረውን የቱሪዝምና ሆቴል ሳምንት እና የባህል ቀን አስመልክቶ በሴት ተማሪዎች መካከል ሁለተኛውና የመጨረሻው ዙር የቁንጅና ውድድር(Miss Debark University)የተካሄደ ሲሆን ውድድሩን የ2ተኛ ዓመት የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ተማሪ ማህደር ገብረሃና በአንደኝነት አጠናቅቃለች።
ሰኔ 2/2017 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ