
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የባህልና ኪነጥበብ ክበብ ምስረታ መርኃ-ግብር ተካሄደ
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የባህልና ኪነጥበብ ክበብ ምስረታ መርኃ- ግብር የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ መምህራን፣ የአስ/ሰራተኞች፣ ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ታዳሚዎች በተገኙበት ጥር 2/2018 ዓ.ም በይፋ ተካሂዷል።
በምስረታ መርሃ -ግብሩ መግቢያ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አስማማው ዘገዬ (ዶ/ር) የተማሪዎች የባህልና ኪነ-ጥበባት ክበብ ምስረታን ለመታደም የተገኙ አካላትን እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉ ሲሆን፣ የክበቡ መመስረት በዋናነት ተማሪዎች ከመደበኛ የቀለም ትምህርታቸው በተጓዳኝ በግቢ ቆይታቸው ያላቸውን ልዩ የኪነጥበብ ተሰጥኦ እንዲያዳብሩ ለማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሁንእንጂ የክበቡ ምስረታ ዓላማ ባህልና እሴቱን የሚያከብር ፤ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የታነጹ ምሩቃንን ለማፍራት ዩኒቨርስቲው እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ እንደሆነ ገልጸዋል ። ከዚህ በተጨማሪ የክበቡ ምስረታ የመማር ማስተማር ስራችን ፍጹም ሰላማዊና ተወዳጅ እንዲሆን ለማስቻል ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
በመድረኩ የዩኒቨርሲቲያችን የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ፤ የአማርኛ ትምህርት ክፍል እና በተማሪዎች ሕብረት ጽ/ቤት በጋራ የተዘጋጀው የባህልና ኪነጥበብ ክበቡ መመስረቻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በቀረበው ሰነድ ላይ የባህልና ኪነጥበብ ክበቡ ዋና ዓላማ፣ ተግባር ፣ አስፈላጊነቱ፣ ተሳታፊዎችና ባለድርሻ አካላት፣ አስፈላጊ ግብዓቶችና የአስተባባሪ አካላት የስራ ድርሻና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በዝርዝር ቀርበዋል። በቀረበው ሰነድ ላይ እና በክበቡ መከናወን ስላለባቸው ቀጣይ ስራዎች ዙሪያ ከታዳሚዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፤ በቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያቶች ላይ የማጠቃለያ ንግግርና አቅጣጫ የሰጡት የዩኒቨርስቲው አመራሮች በራስ ተነሳሽነት ለክበቡ መመስረት ጉልህ ሚና የተጫወቱ የአማርኛና ስነ-ጹሁፍ ት/ት ክፍል መምህራንና የተማሪዎች ህብረት ጽ/ቤትን አመስግነው በቀጣይም ክበቡ እንዲጠናከር እንደ ተቋም አቅም በፈቀደ መልኩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል ። አመራሩ አክሎም የዩኒቨርስቲው የባህል ማዕከል ለመመስረት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አስታውሰው፤ የዛሬውን ጅምር ስራ ተቋማዊ ከማድረግ አንጻር የባህል ማዕከሉ ምስረታ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል በማለት ሀሳብ ሰጥተዋል ።
በምስረታ መርሃ ግብሩ ተማሪዎች ባቀረቧቸው የተለያዩ ኪነ- ጥበባዊ ስራዎች የደመቀ ሲሆን በስተመጨረሻም በባህልና ኪነጥበባት ዘርፍ ኪናዊ ስራዎችን በማቅረብ የላቀ ተሳትፎ ሲያደርጉ ለቆዩ ተማሪዎች የእውቅና የምስክር ወረቀት በመስጠት የዕለቱ መርሃ ግብር ተጠናቋል።
ጥር 2/2018 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ


