ለምስጉን መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች እውቅና ተሰጠ
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በ2017 ዓ/ም በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ምስጉን መምህራን እና አስተዳደር ሰራተኞች ታህሳስ 18/2018 ዓ.ም የምስጋና መርሃ-ግብር በማዘጋጀት እውቅና ሰጥቷል፡፡
በዚህ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀ የምስጋና እና እውቅና መርሃ-ግብር የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ስራ አስፈፃሚዎች፣ ዳይሬክተሮችና ዲኖች ፣ አስተባባሪዎች፣ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ ቡድን መሪዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡
መርሃ-ግብሩን አስመልክቶ ዶ/ር አስማማው ዘገዬ (የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት) ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በንግግራቸውም በመርሃ- ግብሩ የተገኙ መምህራንን፣የአስተዳደር ሰራተኞችንና አመራሩን በሙሉ እንኳን አደረሳችሁ፣ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በሀገራችንም ይሁን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ስኬታማ ከሆኑ ተቋማት ጀርባ ትጉህ ሰራተኞችና ቆራጥ አመራሮች መኖር ወሳኝ መሆናቸንውን አስታውሰው በመሆኑም ዩኒቨርስቲያችንም ይህንን በመገንዘብ ይህ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ መርሃ-ግብር
ለትጉህ እና በስራ አፈጻጸማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሰራተኞቻችንና አመራሮቻችን እውቅናና ሽልማት ለመሰጠት የተዘጋጀ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ መጋቢት 8/2007 ዓ.ም መሰረተ ድንጋይ ተቀምጦለት በአዋጅ ተመስርቶ፣ 2010 ዓ.ም ጥር ወር ላይ በውስን የሰው ኃይል ስራ መጀመሩን ያሳታወሱት ፕሬዚደንቱ፤ በሶስቱም መሰረታዊ ተልዕኮዎቹ (በመማር-ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት) በርካታ ተግባራትን በውጤታማነት እያከናወነ የመጣ ቢሆንም የማትጊያና የእውቅና ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ምክንያት በሰራተኞች መካከል ስራን ማዕከል ያደረገ የውድድር መንፈስ እንዳልዳበረ በመጥቀስ ይሁን እንጂ ከዛሬ ጀምሮ የማትጊያና የእውቅና ሥርዓታችን በየዓመቱ እንደሚተገበር አረጋግጠዋል፡፡
የአገሪቱን እና አካባቢውን ባህል በተላበሱ የዋልያ ሙዚቃ ባንድ አባላት ባህላዊ ውዝዋዜ ታጅቦ የተካሄደው፤ ይህ የምስጉን መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች የእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት ከሞላ ጎደል መድረስ ላለባቸው ምስጉን አካላት እንዲደርስ ማስፈፀሚያ መመሪያ ተዘጋጅቶለት ፤ የራሱ የሆነ ኮሚቴ ተቋቁሞለት ሲሰራ መቆየቱ ታውቋል፡፡ የተዘጋጀው ማስፈፀሚያ መመሪያ በአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የኮሚቴው አባል በመ/ር ሰዋለም ሙሉዩ አማካኝነት ግልፅ ተደርጓል፡፡
በተዘጋጀው መመሪያ መሰረት ተመዝነው በየዘርፉ ለተመረጡ አካላት የማትጊያ ሽልማት እና የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመጨረሻም የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጅ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ጋሻው ግስሙ (ዶ/ር) መዝጊያ ንግግር አድርገዋል፡፡
ዶ/ር ጋሻው ባደረጉት ንግግር እንደ ሀገር ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ እንዲሆኑ አቅጣጫ መሰጠቱን አውስተው፤ ደባርቅ ዩኒቨርሲቲን በሚፈለገው መጠን ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ጉልህ አስተዋፅኦ ለሚያበረክቱ ምስጉን መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች እውቅና የመስጠቱ ሂደት መመሪያ ከመከለስ ጀምሮ በጥብቅ ሥነ-ስርዓት እየተመራ በቀጣይነት ይሰራል ብለዋል፡፡
ታህሳስ 19/2018 ዓ.ም
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ








