
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን መኖሪያ አፓርትመንቶችን በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ
ዩኒቨርሲቲው ሶስት ዘመናዊ የመምህራን መኖሪያ አፖርትመቶችን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ መምህራንና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተገኙበት ግንቦት 23/2017 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል።
በምረቃው ስነ ስርዓት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማማው ዘገየ ዩኒቨርሲቲያችን ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም መምህራን በተመቻቸ ሁኔታ ተረጋግተው እንዲሰሩና ዩኒቨርሲቲው ምርጫቸው እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀው፤ በዚህም ዩኒቨርስቲው ለመምህራን ቅድሚያ በመስጠት ዘመናዊ የመምህራን መኖሪያ አፓርትመንቶችን አስገንብቶ በዛሬው እለት አስመርቋል ብለዋል። በዛሬው ርክክብ ከ50 ፐርሰንት በላይ የሚሆኑ መምህራንን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ዶ/ር አስማማው አክለው ገልፀዋል።



የእለቱ የክብር እንግዳ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ረዳት አማካሪ አቶ ባንቲ መኮንን የመኖሪያ ቤቶቹ ተሰርተው መጠናቀቃቸው የመምህራንን የቤት ችግር ከመቅረፍ ባሻገር የዩኒቨርስቲው መምህራን ተልእኮቸውን ለመወጣት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ሲሉ ገልፀዋል።
በዛሬው እለት ለመምህራን የተላለፉት አፓርትመንቶች ግንባታ በአጠቃላይ ከ570 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ሲሆን ህንፃዎቹ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸው ተገልጿል። የመኖሪያ ቤቶቹ አጠቃላይ 216 ክፍሎች ሲኖሯቸው ባለሶስት፣ ባለ ሁለትና ባለ አንድ መኝታ ሆነው በውስጣቸው የሳሎን፣ የኪችን፣ የሻወርና መፀዳጃ ክፍሎች ተሟልቶላቸዋል።
ግንቦት 23/2017 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ