
በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ወርክሾፕ ተካሄደ
በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ወርክሾፕ ተካሄደ
በደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ “1st Annual Science and Technology Workshop” መጋቢት 30/2017 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ከደባርቅ ከተማ አስተዳደርና ከሰሜን ጎንደር ዞን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በወርክሾፑ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የአ/ም/ቴክ/ሽግግርና ማ/አገልግሎት ም/ል ፕሬዚዳንት ልዩ ረዳት ዶ/ር መዝገቡ ማንመክቶ ወርክሾፑ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝ በመምህራን እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለማሳየት ያለመ መሆኑን አስታውሰው፤ በሌሎች ኮሌጆች በተመሳሳይ የሚሰሩ ስራዎች ለእይታ መቅረብ እንዳለባቸው በአፅኖት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በዋናነት ባዘጋጀው በዚህ ዓመታዊ ወርክሾፕ በኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል መምህራን የተፈጥሮ ግብአቶችን በመጠቀም የተዘጋጁ ለንፅህና መጠበቂያ የሚውሉ የተለያዩ ሳሙናዎች፣ሳኒታይዘሮች እና ሽቶዎች እንዲሁም በኤክሲሬይ ምስል ኒሞኒያ በሽታን ለማረጋገጥ የሚያግዝ በኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህራን የበለፀገ ሞባይል አፕሊኬሽን ሶፍት ዌር ለእይታ ቀርበዋል፡፡ከዚህ በተጨማሪ ከሁለቱም ትምህርት ክፍሎች በወርክ ሾፑ የቀረቡ ስራዎችን ሂደት የሚገልፁ ጽሁፎች ቀርበዋል፤ፓናል ውይይትም ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ መጨረሻ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማማው ዘገዬ በሂደቱ የተሳተፉ አካላትን በማመስገን፤ በወርክሾፑ ለእይታ የቀረቡ ምርቶችን ጥራት እና ደረጃ የበለጠ በማሻሻልና በማስፋት ምርቶቹን ከማስተማሪያነት ባለፈ ወደ ገበያ ለማቅረብ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
መጋቢት 30/2017 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ