
የሰሜን ተራሮችና አካባቢው ላይ ያተኮረ የጥናት ማዕከል ለማቋቋም ያለመ ውይይት ተደረገ
በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ፣ የምርምርና ትብብር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የሰሜን ተራሮችና አካባቢው ፀጋና ተግዳሮቶች ላይ በትኩረት የሚሰራ የጥናት ማዕከል ለማቋቋም ያለመ ውይይት ትላንት መስከረም 22/2018 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተገኙበት ተካሄዷል ።
ዶ/ር አስማማው ዘገዬ (የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት) በውይይቱ መክፈቻ ዩኒቨርስቲው በመማር-ማስተማር በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፈብዙ ተግባራትን እየከወነ ያለ ተቋም መሆኑን አስታውሰው፤ ስነ ምህዳራዊ፣ ሳይንሳዊና ባህላዊ እሴት ባለቤት የሆኑት የሰሜን ተራሮችን ያማከለ የምርምር ማዕከል መቋቋሙ ወቅታዊና ስትራቴጂካዊ ነው ብለዋል ። ማዕከሉ ጥናትና ምርምርን እንዲሁም ትብብርን መሠረት በማድረግ በሰሜን ተራሮችና አካባቢው ያለውን እምቅ ተፈጥሮ ሃብትና ጸጋ ለማልማት የሚሰራ ይሆናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
በመርሃ-ግብሩ የአለም አቀፍ ፣ ምርምርና ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመ/ር ማረው አበበ የማዕከሉን ዓላማና ተልዕኮዎች ፣ስያሜ፣መዋቅር፣የሚጠበቁ ውጤቶች፣ ማዕከሉ ቢቋቋም በአጋርነት ሊሰሩ የሚችሉ ሀገር እና አለምአቀፍ ተቋማት በአጭሩ የሚያስቃኝ መነሻ ፅሁፍ አቅርቧል፡፡
ተሳታፊ መምህራን በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ማዕከሉን ለማቋቋም የሄደበትን ርቀት አድንቀው የተዘጋጀው መነሻ ሰነድ በባለሙያዎች ይበልጥ ዳብሮና ተጀራጅቶ ለቀጣይ ውይይት እንዲቀርብ ጠይቀዋል። አክለውም ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ፀጋዎችን መዳረሻ አድርጎ የተመሰረተ እንደመሆኑ የማዕከሉ ምስረታ የዘገየ ቢሆን እንጂ በአስፈላጊነቱ የሚያጠራጥር አለመሆኑን ጠቅሰዋል ። በመጨረሻም
በመድረክ የተነሱ አስተያየቶች ተካተው በተቻለ ፍጥነት ወደ ተግባር መግባት የሚቻልበት ስራ እንዲሰራ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
መስከረም 23/2018 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ