
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የስራ ፈጠራ ሳምንት (Entrepreneurship week) እያከበረ ይገኛል
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እና በቢዝነስ ኢንኩቤሽን ማዕከል አስተባባሪነት ‘ስራ ፈጠራ ለእድገት፤ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ መንገዱን ይመራል!’ (‘Entrepreneurship for Growth, Debark University Leads the Way!’) በሚል መሪ ቃል ከህዳር 26/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚዘልቅ የስራ ፈጠራ ሳምንት እያከበረ ይገኛል፡፡
በዚህ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከበረው በዓይነቱ ለየት ያለ የስራ ፈጠራ ሳምንት አከበባር መክፈቻ መርሃ-ግብር መምህራን፣ከዳበርቅ ወረዳ ስራና ስልጠና ጽ/ቤት እና ከደባርቅ ከተማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተጋበዙ እንግዶች እንዲሁም የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች ታድመዋል፡፡
በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአካዳሚክ፣ምርምር፣ቴክኖሎጅ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ጋሻው ግስሙ /ዶ/ር/ መርሃ-ግብሩን በማስተባበር ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበው፤የዘመኑን የመማር-ማስተማር ስርዓት ከመደበኛው ሂደት በተለየ በአጫጭር ተግባር ተኮር ስልጠናዎች ማገዝ ተማሪዎችን ስራ ፈጣሪ ለማድረግ የማይተካ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በመርሃ-ግብሩ በርካታ ተግባራዊ ክንውኖች እንደሚኖሩ ጠቅሰው፤ተሳታፊዎች በተለይም ተመራቂ ተማሪዎች ተሰጦዎቻቸውን በመውጣት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም አቶ ይበልጣል ኤሊያስ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሰት የፈጠራ ስራ ልማት ተቋም አስተባባሪ (Entrepreneurship Development Institution Coordinator) በስራ ፈጠራ ፅንሰ ሀሳብ እና እንደ ሀገር የተሰጠውን ትኩረት የሚመለከት ንግግር በበይነ መረብ አድርገዋል፡፡
በተያያዘ ከህዳር 27-28/2018 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ስልጠና በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህራን አማካኝነት ለሁሉም ተመራቂ ተማሪዎች እየተሰጠ ነው፡፡
የሥልጠና መርሃ-ግብሩ በደባርቅ ከተማ አስተዳደር ስራ ፈጣሪዎች ልምድና ተሞክሮ ልውውጥ እንደሚታገዝ ከአስተባባሪዎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ህዳር 27/2018 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ



