
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ፣የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሶስትዮሽ የስምምነት ፊርማ ተፈራረሙ
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ለማልማት እና ለመጠበቅ በሚያስችል ውይይት በመሳተፍ ላይ ነው። ውይይቱ የተዘጋጀው በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ሲሆን ደባርቅ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የቱሪዝም ሚኒስቴር ፣ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን መሳተፋቸው ለማወቅ ተችሏል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማማው ዘገየ እና የአካዳሚክ ም/ቴክ/ሽግግርና ማ/ሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጋሻው ግስሙ ሲሆኑ በመድረኩ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በኃላም በጦርነትና ግጭት ምክንያት ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ ፤ በፓርኩ ውስጥ ብቻ የሚገኝው ብርቅዬው ዋልያ አይቤክስም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕገ-ወጥ አደን ምክንያት ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ሲሆን በመሆኑም ፓርኩን ወደነበረበት ደረጃ ለመመለስና ለማልማት ሁሉን አቀፍ የርብርብ ስራ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር አስማማው በአፅንኦት ተናግረዋል ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የፓርኩን መሠረተ ልማት ደረጃውን የጠበቀና አለምአቀፍ ቱሪስቶችን የሚመጥን ለማድረግ እና በፓርኩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ለመሳተፍ ዩኒቨርስቲው ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ጋሻው ገልፀዋል ። ቱሪዝም አንዱ የዩኒቨርስቲው የትኩረት መስክ እንደመሆኑ ፓርኩን መልሶ ለማልማት እና የቱሪስት ፍሰቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፌዴራል ቱሪዝም ሚኒስትር እና ከክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን በርካታ ምክክሮች ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይታወቃል።
ትላንት ሰኔ 19/2017 ዓ/ም በተካሄደው የማጠቃለያ ውይይት የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን መልሶ በማልማትና በመጠበቅ ዙሪያ አቅጣጫዎች እንደተሰጡና የተለያዪ አጋር አካላት በቁርጠኝነት ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ታውቋል። በመድረኩ ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ፣የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሶስትዮሽ ስምምነት በመፈረም በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፖርክንና በውስጡ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳቶችና እፅዋቶችን ለማልማትና ለመጠበቅ ወደስራ ለመግባት እንደተዘጋጁ አሳውቀዋል ።
ሰኔ 20/2017 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ