
የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ስራ አፈፃፀም ተገመገመ
ዩኒቨርሲቲው የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ስራ አፈፃፀም በአዲስ የተመደቡት የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች፣ዳይሬክተሮች፣ዲኖች፣ስራ አስፈፃሚዎች፣ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ አስተባባሪዎች፣ ቡድን መሪዎች እና ባለሙያዎች በተገኙበት ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም በጥልቀት ገምግሟል፡፡
በግምገማው መርሃ ግብር መጀመሪያ ላይ የዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማማው ዘገዬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በበጀት ዓመቱ የቁልፍ ተግባራት አፈፃፀም በየጊዜው እየተገመገመ መምጣቱን አስታውሰው ፤በግምገማዎች መረዳት እንደሚቻለው ተቋሙ በሁሉም ዘርፍ የለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኑን አስታውሰዋል:: ይሁን እንጂ በዚህ ውድድር በበዛበት ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ የከፍተኛ ትምህርት መድረክ ውጤታማና ተወዳዳሪ ተቋም ለመገንባት ብዙ ርብርብ የሚጠይቁ ስራዎች ይቀራሉ ሲሉ አክለው ገልፀዋል፡፡


በመርሃ-ግብሩ በመማር-ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጅ ሽግግር፣በአገልግሎት አሰጣጥ እና በቁልፍ ተግባራት አፈፃፀም አመልካቾች ዙሪያ ተቋሙ ያለበትን የአፈፃፀም ሁኔታ የሚያሳዩ መረጃዎች እንዲሁም የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የድጋፍና ክትትል ሱፐርቪዥን ኮሚቴ በአካዳሚክ እና በአስተዳደር ዘርፎች በተመረጡ 20 የስራ ክፍሎች የስራ እንቅስቃሴ የሚያስቃኝ ሪፖርት ቀርቧል፡፡
በሁለቱም ሂደቶች በቀረቡት ሪፖርቶች መነሻነት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይት ስርዓቱ የተቋሙን ቀጣይ ሁኔታ የሚወስኑ ሀሳቦች እና አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ለተነሱ ጥያቄዎች በየሚመለከታቸው ስራ ክፍሎች ምላሽ እና ማብራሪያ ከተሰጠባቸው በኋላ፤ በከፍተኛ አመራሮች ማጠቃለያ ተሰጥቶባቸው መርሃ-ግብሩ ተጠናቋል፡፡
ሚያዝያ 11/2017 ዓ.ም
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ