የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አጭር ታሪክ
በኢትዮጵያ ከሚገኙ አስራ አንድ አራተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ፣ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 350/2008 ‘ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ’ በሚል ስያሜ ተቋቋመ፡፡ በዚህ መሰረት፣ የካቲት 8/2008 ዓ.ም የቀድሞው የሃገራችን ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማሪም ደሳለኝ፣ ሰባቱ ከዘራ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ እና ሌሎች ባለስልጣናት በተገኙበት የዩኒቨርሲቲው ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ለመጎብኘት የሚመጡ ብዙ ቱሪስቶች መዳረሻ እና የሰሜን ጎንደር ዞን መናገሻ ደባርቅ ከተማ ተቀመጠ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከአዲስ አበባ በ834 ኪሎ ሜትር፣ ከባህርዳር በ284 ኪ.ሜ እና ከጎንደር በ103 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የግንባታ እና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው በ2010 ዓ.ም በአራት (4) ኮሌጆች እና በአስራ ሰባት (17) የትምህርት ክፍሎች በአንድ ሽህ አንድ መቶ ሰባ ሶስት (1173) ተማሪዎች፣ የመማርና ማስተማር፣የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጅ ሽግግር ስራውን ጀምሯል።

በደጋ አካባቢ እንዲሁም በርካታ የእፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎችን በያዘው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አቅራቢያ ላይ መገኘቱ ያለውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ዩኒቨርሲቲው በግብርና እና ቱሪዝም መስኮች የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ ይሰራል። ከዚህም በላይ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ተቋሙ በቱሪዝም የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ በርካታ ባህላዊ ቅርሶች አሉ።
በአሁኑ ወቅት ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ከ400 በላይ መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች፣ዘጠኝ(9) አጀንክት ፕሮፌሰሮች፣ ከዘጠኝ መቶ(900) በላይ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ እና ከአምስት ሽህ በላይ(5000) ተማሪዎችን፣ አምስት(5) ኮሌጆች እና አንድ(1) ትምህር ቤትን (የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ፣ ተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ፣ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፣ ግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ፣ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ የህግ ትምህርት ቤት)፣ እና ሰላሳ ሶስት(33) ትምህርት ክፍሎችን በመያዝ ስራውን እያከናወነ ይገኛል።